እህት ሐና ታደሰ

የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው መዝሙር 116፡15


የእህት ሐና ታደሰ አጪር ህይወት ታሪክ

እህት ሐና ታደሰ ከአባቷ ከአቶ ታደሰ ተገኝና ከእናቷ ከወይዘሮ ዘውዲቱ መንግስቱ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ታህሳስ 23 ቀን 1967 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደች፡፡ዕድሜዋ ለትምሕርት እንደደረሰ አንደኛ ደረጃ ትምሕርቷን በብርሃነ ዛሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ቦሌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተማረች በኋላ በ1988 ዓም ወደ ሆላንድ አገር መጥታ መኖር ጀመረች፡፡በዚህ በሆላንድ ቆይታዋ በረዳት ነርስነት ትምሕርት በመከታተል በዲፕሎም ተመርቃለች፡፡

 

ከዚያም ዛል ቦሙል በሚባል ከተማ በሚገኝ ቪለቫል የአዛውንቶች መንከባቢያ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ወደ እንግሊዝ አገር እስከሄደችበት እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ በታማኝነት ስትሰራ ቆይታለች፡፡ እህት ሐና በዚህ መስሪያ ቤት በሰራችባቸው 7ዓመታት ውስጥ በስራ ባልደረቦቿ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበራት እህት ነበረች፡፡የስራ ባልደረቦቿ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን ሲሰሙ በየእለቱ እየደወሉ በማልቀስና በማዘን ልባዊ ሃዘናቸውን የገለጹ ሲሆን ይህም እህት ሃና በወገኖቿ ኢትዮጵውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዜጎች ዘንድ ተወዳጅነት የነበራት እህት እንደነበረች ያረጋግጣል፡፡

በእንግሊዝ አገር መኖር ከጀመረችበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ኮፐር ሂል ሬዚዴንሻል ኤንድ ነርሲንግ ሆም በተባለው ድርጅት ተቀጥራ ሕይወቷ እስካለፈችበት ቀን ድረስ ስታገልግል ቆይታለች፡፡

አህት ሐና ጌታን ገና በ12 ዓመት ዕድሜዋ የተቀበለች ሲሆን በእምነቷ ጽኑና ተግባራዊ የክርስትና ሕይወት የነበራት ከሩቅ የሚታይና የሚያንጸባርቅ የክርስትና ሕይወት ያላት እህት ነበረች፡፡

እህት ሐና ሰውን የመርዳት በተለይም በጌታ የሆኑትን ሁሉ ባላት ነገር ሁሉ የመደገፍና የመርዳት ልዩ ጸጋና የተከፈተ ልብ የነበራት እህት ነበረች፡፡ለዚህም ከዚህ ዓለም በሞት የመለየቷ ዜና እንደተሰማ ከደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ከግብጽ ከህንድና ከተለያዩ አገሮች ካሉ በርካታ ወገኖች እህታችን ያደረገችውን መልካም የፍቅር አገልግሎት በማስታወስ በእንባ እየታጠቡ ሃዘናቸውን በስልክና

በኢንተርኔት መስመር በተከፈተው የፓልቶክ ድረ ገጽ የሰጡት ምስክርነት በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡

እህት ሐና ጌታን እያገለገለች ቅዱሳንን እየደገፈችና እየረዳች በፈገግታዋ እያጽናናችና እያበረታታች በመፍትሔ ፈላጊነትዋ የቀረቧትን ሰዎች ሁሉ ልብ እየሳረፈች በመመላለስ ላይ እያለች በደረሰባት ድንገተኛ አደጋ ማርች 16 ቀን 2008 ዓም በእንግሊዝ አገር በሊድስ ከተማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡

እህት ሐና ታደሰ በለጋ ዕድሜዋ ከመካከላችን መለየቷ እጅግ አስደንጋጭና ልንሸከመው ያልቻልነው መሪር ሃዘን ቢሆንብንም ከልጅነት ጀምሮ በታመነችውና በተከተለችው ጌታዋ ዕቅፍ ውስጥ መሆኗን በመረዳት እንጽናናለን፡፡

በከርስቶስ ኢየሱስ ሆነው የሚያንቀላፉ ተስፋ ያላቸው ለነሱ ሞት ወደ ህይወት የመሸጋገሪያ በር እንጂ አንቆ ሊያስቀር የማይችል የተሸነፈ በመሆኑና ሞትን ያሸነፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ሕያውና የሆነና እህታችንንም በእቅፉ የተቀበለ በመሆኑ በዚህ እንጽናናለን፡፡ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በቃሉ ሲናገር ”እኔ ትንሳኤና ሕይወትነኝ በኔ የሚያምን ቢሞት እንኳን ሕያው ይሆናል” ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11፡25 ብሏል

እህት ሐና ገሊላ ጌቱ የተባለች የ10 ዓመት ልጅዋን ትታ የሚወዷትን ቤተሰቦቿን ተነጥላ መሄዷ በስጋ ቢያሳዝንም የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና ዕውነት እንዲሁም ዘለዓለማዊ ስለሆነ እህታችን ሐና ዛሬ በስጋ ብትለየንም በመንፈስ ደግሞ ሕያው ስለሆነችና በጌታ ቀን ስለምንገናኝ በዚህ እንጽናናለን፡፡

በዚህ ቀን ለእህት ሐና ቤተሰቦች እግዚአብሔር መጽናናትን እንዲሰጥ ጸሎታችን ነው