ፓስተር አቤል ገብሬ

የፓስተር አቤል ገብሬ አጭር የሕይወት ታሪክ


ሴፕቴምበር 27 2008 በሔልሲንኪ ፊንላንድ በተደረገው የመሰናበቻ ፕሮግራም ላይ ከተነበበው የሕይወት ታሪኩ የተወሰደ

ጌታ ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት ትንሳኤና ህይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ እንኳን ቢሞት ህያው ይሆናል ህያው የሆነም የሚያምንብኝም ለዘላለም አይሞትም ነው ብሎ የነገረን፡፡ወንድማችን ፓስተር አቤልም በትምርቶቹም ሆነ በዝማሬዎቹ ዘላለማዊነትን ህያውነትን አስረግጦ ነበር የሚናገረው;;ዛሬ በተራው ወደ ሚወደው ጌታ ቢሄድም ዛሬም መልክቱ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ነው

ፓስተር አቤል ገብሬ 1960 ዓ.ም በወሎ ጠቅላይ ግዛት ተወልዶ ዕድገቱንና መኖሪያውን ያደረገው ግን በአዲስ አበባ ነው፡፡ዕድገቱ በአጎቱ ቤት ቢሆንም ከምስክርነቱ እንደተረዳነው ብዙ ጊዜ የኖረውና ልጅነቱን ያሳለፈው እራሱን እየረዳ በራሱ እንደነበር ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ቀን በሚገርም ሁኔታ በእስር ቤት እንዲገባ ሆነ በእስር ቤትም ግማሹ በወንጀል የገባ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ ጌታን በማመናቸው በዛ በእስር ቤት የነበሩ ወገኖች ጌታን በእስር ቤት እያሉ ሲመሰክሩለት እንኳን የያንዳንዱ ክርስቲያን ፈገግታ የያንዳንዱ ክርስቲያን ህይወት ይማርከው እንደነበር ብዙ ጊዜ ይመሰክር ነበር;;

ከዛም በእስር ቤት እግዚአብሔር በልዩ መንገድ እንዳገኘውና ፓስተር ግርማ ቦጋለ በዚያን ጊዜ ወንጌላዊ በእምነቱ እንዲጠነክር እግዚአብሔር እንደተጠቀመበት መስክሮአል;;ላገኘውም ጌታ እንዲህ ብሎ ዘምሯል፡፡ያለፉትን ቀኖቼን ሁሉ ዞሬ ስመለከት

አሳየኝ ፍቅር ጌታን ሚዛን አጣሁለት

ታማኝ ሆኖ አቅፎ ላቆመኝ ክንድህ

ቁርባኔን ተቀበል ክበርልኝ ስልህ

ሰውነቴ ጠፍቼ አልቀረሁም ብላ እንድትመሰክር

በጸጋህ ሰጥተሃታልና የዘለዓለም ክብር

በእስር ቤት ቆይታው እግዚአብሔር ለሱ በሚገባው መንገድ ተናግሮት ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር ሌላ እንዳያነብ ቃል በመግባቱ በጥቂት ጊዚያት እግዚአብሔር አሳድጎት መዝሙርም ሰጥቶት ጊታርም መጫወት ችሎ ከእስር ቤት ወጣ;; ከእስር ቤትም አንደወጣ በብዙ ወገኖች ፍቅርና እንክብካቤ ውስጥ ሆኖ አገልግሎቱን ቤት ለቤት ጀመረ;; በዚያን ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን የነበረው ስርአት አስዘግቷቸው ስለነበረ ወገኖች የሚያመልኩት በየቤቱ ነበር;; ፓስተር አቤል በመሰጠት በከተሞችም በገጠርም እየተዘዋወረ ከወገኖች ጋር ወደ ፊንላንድ እስከመጣበት ዕለት ድረስ አገልግሏል፡፡

ፓስተር አቤል በተፈጥሮው አስተዋይና በእጆቹ ብዙ ነገሮችን መሳል መቅረጽ ማነጽ ይችል ስለነበረ በኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜ በእጁ ሰርቶ ሐዋርያው ጳውሎስ ድንኳን እየሰፋ ያገለግል እንደነበር የሚያገኘውን ገንዘብ ሁሉ በእምነታቸው ምክንያት በስደት ያሉትን ወንድሞች ሰብስቦ አብሮ በመኖር በመርዳትና በተረፈው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እየገዛ ያድል እንደነበር የሚያውቁት ትዝታ ነው፡፡
 
በኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ለጥቂት ጊዜያት የሰራ ሲሆን ወደ ፊንላንድ ከመምጣቱ በፊት በኖርዌጂያን ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ድርጅት ውስጥ ይሰራ ነበር፡፡

እግዚአብሔር ደግሞ በ1989 ዓ.ም ወደ ፊንላንድ በር ከፍቶለት ጌታ እንዴትና በምን መንገድ እንደሚያገለግል በግልጽ ነግሮት እንደመጣ መስክሮልናል፡፡ ይህም ድግሞ ለአገልግሎቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነበረው፡፡ ወደ ፊንላንድ እንደመጣ እግዚአብሔር ቀደም ብሎ ጀምሮት ለነበረው አገልግሎት በወንጌላዊነት ወደ ትልቅ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል;;

እግዚአብሔር የሰጠውንም ትምህርትና ዝማሬ ጥቂት ለነበሩ ወገኖች በማካፈል የዝማሬ አገልግሎት በወገኖች ቤት ውስጥ እንዲጀመር አድርጎ በፊንላንድ ያለች ቤተክርስቲያን እንድትጠነክር ሌት ተቀን ሰርቷል;;ትንሽ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደ ጠንካራ ህብረት እንዲለወጥ ጌታ ተጠቅሞበታል;;

ይህንንም ያዩ የፊንላንድ ወገኖች በ1991 በወንጌላዊነት እንዲያገለግላቸው ወስነው ይህንንም ስርዓት ፓስተር ሃይሌ ተገኝተው እንዲያስፈጽሙ በተጠየቁት መሠረት ስርዓቱን አከናውነው ይህም አገልግሎቱ እንዲሆን ተደርጎ እስከ 2005 ዓ..ም በወንጌላዊነት አገልግሏል;; ከዚያም በ2005 የፊንላንድ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አባላት ፓስተር ሆኖ እንዲያገለግል በሙሉ ድምጽ በማጽደቃቸው ፓስተር ዳንኤል መኮንን ተገኝተው የመጋቢነቱን የሹመት ስርዓት አከናውነዋል፡፡ ፓስተር አቤል ገብሬ ወደ ጌታ እስከሄደበት ድረስ ፓስተር ሆኖ አገልግሏል፡፡

ፓስተር አቤል በቤተሰብ ህይወቱ በ1991 እህት አንን አግብቶ 3 ወንድ ልጆችን ወልዷል፡፡ እግዚአብሔር በሰጠው ዘመን ውስጥ እስካንቀላፋበት ጊዜ ድረስ ቤተሰቡንና ቤተክርስቲያንን በታማኝነት አገልግሎ በተወለደ በ48 አመቱ አንቀላፍቷል፡፡https://www.youtube.com/watch?v=0l2NCFTv6hg